“የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራ ነው”
የቦሌ ክፍለ ከተማ በአንድ ጀምበር 2 ሺ የሥራ ዕድል ፈጠራ ንቅናቄ ፕሮግራም ተካሄደ፡፡
ከ250 በላይ ቀጣሪ ድርጅቶች እና 2ሺ ሥራ ፈላጊ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች በተሳተፉበት በዚህ የንቅናቄ መድረክ ላይ የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የሥራና ክህሎት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ኢየሩሳሌም አሰፋ ባደረጉት ንግግር ባለፉት የለውጥ ዓመታት ክህሎትን መሠረት ያደረገ የሥራ ዕድል ፈጠራ እንቅስቃሴ አመርቂ ውጤቶች ማስመዝገቡን አውስተው፣ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አራት ወራት ለ11,839 ሥራ ፈላጊ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አመልክተዋል፡፡ የአንድ ጀምበር የሥራ ዕድል ፈጠራ ንቅናቄው ለ2 ሺ ወገኖች በተለያዩ መስኮች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ያስታወቁት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ንቅናቄው ግቡን እንዲመታ በፈቃደኝነት ተሳትፎ ላደረጉ ባለሀብቶችና ተቋማት ምስጋና በማቅረብ በቀጣይም የወጣቶችና የሴቶችን ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ አስተዳደሩ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ መሥፍን ኃይሌ በበኩላቸው የወጣቶችና የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የቦሌ ክፍለ ከተመሰ አስተዳደር በስፋት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው፣ በዚህም ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡ “ዛሬ የሥራ ዕድል የተፈጠረላችሁ ወገኖቻችን የሥራን ክቡርነት ተረድታችሁ በምትሠማሩበት የሥራ መስክ ጠንክራችሁ በመሥራት ራሳችሁን መለወጥ ይጠበቅባችኋል” ያሉት አፈ ጉባኤው፣ የሥራ ዕድል ተጠቃሚዎች ከራሳቸው አልፈው ለቤተሰብና ለሀገር ጠቃሚ ዜጋ በመሆን የተጀመረውን የማንሰራራት ጉዞ ለማስቀጠል የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች እና ቀጣሪ ባለሀብቶች በሰጡት አስተያየት የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ሥራና ሠራተኛን በማገናኘት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መድረኩን በማመቻቸቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በስደት የቆዩ እንዲሁም መንግሥት ባመቻቸው ዕድል ተደራጅተው ሲሰሩ የቆዩ መሆናቸውን የገለጹት የቀጣሪ ድርጅቶች ባለቤቶች፣ አሁን ላይ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሥራ ዕድል ለመፍጠር መቻላቸውን በመግለጽ በንቅናቄው የመለመሏቸውን ሥራ ፈላጊዎች በክህሎት በማብቃት ብቁና አምራች ዜጋ ለማድረግ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡ ሥራ ፈላጊ ወጣቶችና ሴቶችም በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል በትጋት በመሥራት ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ኅዳር 4/2018

