ከሁሉ አስቀድሜ ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት እንዳንጠቀምበት የተደረገው የአባይ ጉዳይ በታሪክ እጥፋት በብልፅግና ትውልድ ፣ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በሳል አመራር ሰጪነት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ በአዲስ ዘመን መባቻ በመመረቁ የተሰማኝን የማያባራ ልባዊ ደስታ እየገለጽኩ በወረዳችን ከኢላላ እስከ ድማማ የዋንጫ ቃል ኪዳን ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ የመጣልን አዲስ አመት በኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ላይ በመሆኑ የምንቀበለው በታላቅ ደስታ ፣ በታላቅ ተስፋ እና በብልጽግና መንፈስ ነው ፡፡
የወረዳ አስተዳደሩን በመወከል የአዲስ አመት የመልካም ምኞት መግለጫ መልእክቴን ሳስተላልፍ ከፍ ያለ ክብርና ኩራት እየተሰማኝ ነው ፡፡
እንኳን ለ2018 ዓ/ም አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን ፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 14 አስተዳደር ባሳለፍነው በጀት አመት የወረዳውን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎት መነሻ ያደረጉ የልማት ፣ የሰላምና ፀጥታ ፣ የመልካም አስተዳደር ፣ የስራ እድል ፈጠራና ሌሎችም ትልልቅ የፕሮጀክት ስራዎች ነዋሪዎችን በማስተባበር ከመቼውም ጊዜ በላይ ስኬቶችን በማስመዝገብ የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ አንገብጋቢ ችግሮች እንዲፈቱ የማድረግ ስራወች ተሰርተዋል ፡፡ በተጨማሪም በንቅናቄ ተግባራት በአረንጓዴ ልማት እና በከተማ ግብርና የሰው ተኮር ተግባራት በመደበኛ ክረምት በጎ አድራጎት ስራ ሰፋፊ የንቅናቄ ስራዎችን በመፍጠር በከተማ ደረጃ እውቅና ያገኘንበት ድል የተመዘገበበት የስኬት አመት ነበር ፡፡
የተከበራችሁ ውድ ነዋሪዎቻችን
ጥሩ መአዛ ጽኑ መሰረት፣ ለአንድ ችግር አንድ መትፍሄ፣ እናልብስ የህልም ጉልበት ለሚሰሩ እጆች ፣ የወል ቤቶች ለወል እውነት ለትውልድ መሰረት የሚሉና ሌሎችም የጋራ መሪ ሃሳቦች እንዲሁም ከኢላላ እስከ ድማማ የዋንጫ ቃልኪድን ስምምነቶች በወረዳችን በጣም በአጭር ጊዜ ሃሳቡ ከአጠቃላይ አመራርና ባለሙያ እስከ መላው የወረዳችን ህዝብ ዘንድ እንዲንሰራፋ የማድረግና በሁሉም ተግባራት የላቀ ውጤት እንዲመጣ በማድረግ ተጨባጭ በታሪክ አሻራ የሚሆኑ ስኬቶችን ማስመዝገብ ተችሏል ፡፡
የኢላላ የዋንጫ ቃልኪዳን በወረዳችን ከሰባት በላይ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በመስራት በመደበኛና ወቅታዊ ተግባራት የላቀ አፈጻጸም በማስመዝገብ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ መኪና መሸለማችን ለላቀ ስራ የሚያነሳሳ እና የበለጠ እንድንበረታ አደራ በመሆኑ በአዲሱ አመት ‹‹ድማማ›› ድል የማጽናት እና ማስፋት የዋንጫ ቃልኪዳን ስምምነት በመፈፀም በቀጣይነት ድሎችን እያበሰርን ለማይቀረው የኢትዮጵያ ብልጽግና አሻራችን ከህዝባችን ጋር በትልቁ የማሳረፍ ስራ 24/7 ይሰራል።
ውድ የወረዳችን አመራሮች ፣ ባለሙያዎችና ነዋሪዎች የጀመርነው መንገድ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለህዝባችን ማረጋገጥ በመሆኑ በጋራ ሁላችንም የጀመርነውን ተግባራት አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ በክብርና በትህትና አሳስባለሁ፡፡
በመጨረሻም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ብስራት በኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን የተቀበልነው አዲሱ አመት ከፊታችን ብዙ የድል ብስራቶች የምንሰማበት ስኬቶችን የምናጸናበት እና የምናበዛበት አመት እንደሚሆን እየገለፅኩ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤና፣የደስታና የብልጽግና ዓመት ይሆንላችሁ ዘንድ ልባዊ ምኞቴን እገልጻለሁ ፡፡
አቶ ማንደፍሮ ተመስገን
ቦሌ ወረዳ 14 አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ



